የታጁራ ወደብ የሥራ እንቅስቃሴና የአገልግሎት አሰጣጥ

በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በጅቡቲ የሚገኘውን የታጁራ ወደብ የሥራ እንቅስቃሴና የአገልግሎት አሰጣጥ በሥፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል። በጉብኝቱ ላይ በጅቡቲ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ለገሱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ የወደቡን የኦፕሬሽን አቅምና የቴክኒክ ዝግጁነት በመገምገም፣ ለኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ምርቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል። ልዑኩ ከወደቡ አስተዳደር ጋር ባደረገው ምክክር፤ ቀደም ሲል በጅቡቲ ዋና ዋና ወደቦች ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የጭነት አገልግሎት ወደ ታጁራ ወደብ በማስፋፋት፣ የሎጂስቲክስ አማራጮችን ማብዛትና አገራዊ የጭነት ፍሰቱን ማሳለጥ የጉብኝቱ ስትራቴጂካዊ ግብ በመሆኑ፣ የታጁራ ወደብን ለአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የቴክኒክና የኦፕሬሽን ዝግጁነቶች ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል። የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የአገሪቱን የባሕር ትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ዘርፍ ለማዘመን፣ አማራጭ ወደቦችን በስፋት ለመጠቀም እንዲሁም የተቀላጠፈ የአቅርቦት ሰንሰለት ለመገንባት የሚያደርገውን ዘርፈ-ብዙ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።