ኢባትሎአድ የ2013 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን ለማጓጓዝ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡

ኢባትሎአድ የ2013 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ከመጫኛ ወደብ እስከ ሀገር ውስጥ መዳረሻ ለማጓጓዝ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ውል መገባቱን ተከትሎ ጭነቱን አጓጉዞ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ለማድረስ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የማዳበሪያ ጭነት ከመጫኛ ወደብ ተጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ ሲደርስ ከመርከብ አራግፎ በከረጢት በማሸግ በተሸከሪካሪዎች እየጫኑ ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ከSDTV ድርጅት ጋር ዛሬ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡ SDTV በጅቡቱ ወደብ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት በመስጠት የሚታወቅ ድርጅት ነው፡፡ በዘንድሮ ዓመት ድርጅታችን በመርከብ አጓጉዞ ከሚያመጣው 1.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 660ሺ ሜትሪክ ቶን በSDTV ተርሚናል የሚስተናገድ ሲሆን ቀሪው 1.14 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በDoraleh Multipurpose Port (DMP) ወደብ የሚስተናገድ ይሆናል፡፡ በኢባትሎአድ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የጭነት አስተላላፊነት አገልግሎት ዘርፍ ተጠባባቁ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲራጅ አብዱላሂ ሲሆኑ ስምምነቱ መርከቦች ጅቡቲ እንደደረሱ ገብተው እንዲያራግፉ፣ የተሟላ የሰው ሀይል እና በቂ ማሽነሪዎች ዝግጁ ሆነው ጭነቱን የማራገፍ እና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ውሉ ድርጅታችን በሚያቀርባቸው ተሽከርካሪዎች መጫንን ያካተተ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ለዘንድሮ የምርት ዘመን ባለፈው ዓመት ከተጓጓዘው 1.45 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ጭማሪ በማድረግ 1.8 ሚሊዮን ቶን የአፈር ማዳበሪያው ኢባትሎአድ የሚጓጓዝ ሲሆን የመጀመሪያዋ መርከብ በህዳር ወር መጨረሻ ጅቡቲ ትደርሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሲራጅ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡