በቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ቅ/ጽ/ቤት የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ወረርሽኝን ለመከላከል በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ቅ/ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ የኋላወርቅ ጎሹ ገልጸዋል፡፡ በርካታ ገቢና ወጪ ዕቃዎች የሚስተናገዱበት የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ከቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅ/ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙን የመከላከል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ በተለይ የድንበር ተሻጋሪ ከባድ የመኪና አሽከርካሪዎች ለወረርሽኙ ካላቸው ተጋላጭነት አንጻር የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከመሰጠቱ ባሻገር በጉዞ ወቅት አስፈላጊ የሆነ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማሟላት ስምሪት እየተከናወነ እንደሆነ የቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅ/ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ፎቴ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላለከል በመጋዘን፣ በማሽነሪዎች፣ በኮንቴይነሮችና የሰው እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው በተለያዩ የስራ አካባቢዎች የጸረ-ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት መከናወኑን አስረድተዋል፡፡ ከጅቡቲ ወደ ወደቡ ጭነት ጭነው የሚገቡ ከባድ ተሸከርካሪዎች ወደ ወደቡ ከመግባታቸው በፊት በሦስት መቆጣጠሪያ በሮች ተሽከርካሪዎችን የጸረ-ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት በማከናወን የማጽዳት ስራ እየተሰራ ሲሆን አሽከርካሪዎች፣ ሠራተኞች እና ደንበኞች ወደ ወደቡ ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን በአግባቡ መታጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እና የሰውነት ሙቀት መለካት አስገዳጅ መሆኑን ዳይሬክተሩ ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡